አቶ ሔኖክ፡- የዓለም ኢኮኖሚ ፎረም በአፍሪካ
እጅግ በጣም ጠቃሚ የሆኑና በንግዱ፣
በሲቪል ማኅበረሰቡ፣ በአመራርና በመሳሰሉት የመሪነት
ሚና የሚጫወቱ ሰዎችን የሚያሰባስብ ፎረም
መሆኑ የሚታወቅ ነው፡፡ ፎረሙ ባለው
ዓለም አቀፍ ዕውቅናና ስኬት ምክንያት
በየዓመቱ የሚሳተፉት ተሳታፊዎች በሚቀጥለውም ፎረም
ለመሳተፍ የሚጓጉ ናቸው፡፡ ታዲያ እንደነዚህ
ዓይነት የሰዎች ስብስብ በምታገኝበት ወቅት፣
ይህን በቀላሉ ድጋሚ የማይገኝ ዕድልን
ለመጠቀም መሻት አለብህ፡፡ በእኛም አስተሳሰብ
የዓለም ኢኮኖሚ ፎረም በአፍሪካ በኢትዮጵያ
ለመጀመርያ ጊዜ የሚካሄድ ቢሆንም፣ ዕድሉን
ተጠቅመን ተጨማሪ የውጭ አገር ኢንቨስትመንት
ለመሳብ ካልቻልን የፎረሙ እዚህ መካሄድ
ብቻ ትርጉም ላይኖረው ይችላል፡፡ ስለሆነም
የእኛ ዓላማ በዚሁ የዓለም ኢኮኖሚ
ፎረም ለመሳተፍ ከሚመጡ ተሳታፊዎች ውስጥ
በንግድ ላይ የሚያተኩረውን የተወሰነውን ቡድን
በመውሰድ በኢትዮጵያ ያሉት የኢንቨስትመንትና የንግድ
ሁኔታዎችና ዕድሎችን በሰፊውና በጥልቀት ለማስተዋወቅ
ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ እነዚህ በዓለም
ላይ በኢንቨስትመንትና በንግድ ዘርፍ የሚታወቁ
ሰዎችን በአገራችን በተመሳሳይ ዘርፍ የጎላ
ሚና ከሚጫወቱ የንግዱ ኅብረተሰብ አባላት
ጋር ጥምረት የሚፈጥሩበትን ሁኔታ ማመቻቸት
ነው፡፡
ሪፖርተር፡- እነዚህ የጠቀሷቸው ሰዎች እነማን
እንደሆኑ፣ ዕውቅናቸውንና ጠቀሜታቸውን ቢገልጹልን?
አቶ
ሔኖክ፡- እዚህ ላይ ማለት የምፈልገው
የድሮው የንግድ አሠራር ወደኋላ የቀረ
መሆኑን መግለጽ ነው፡፡ ያም በመሆኑ
አሁን እየሞከርን ያለነው ከሚታወቁ ዓለም
አቀፍ ኩባንያዎች ወይም ተጠሪዎች ጋር
የጎላ ሚና ያላቸውን የአገራችን የንግዱ
ኅብረተሰብ መሪዎችና አባላት ቁርኝት እንዲፈጥሩ
ማስቻል ነው፡፡ እንደ አገር ለመበልፀግ
የምንሻ ከሆነ በዓለም ተወዳዳሪ ለመሆን
የሚያስብና የወደፊት ርዕይ ያለው የንግድ
ኅብረተሰብ ያስፈልገናል፡፡ በአገራችን ካሉ ርዕይ
ካላቸው የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት ጋር
ጥምረት መፍጠር መቻል እንዳለባቸው፣ በዚያውም
ካሁኑ ከውጭ አገር ኩባንያዎች የካፒታል
መጠናቸውን ለማሳደግና ሥራቸውን ለማስፋፋት ተጨማሪ
የፋይናንስ የገበያ ዕድል እንደሚያስፈልጋቸው ከወዲሁ
ተገንዝበዋል፡፡ ስለሆነም የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ፎረም
ዋነኛ ሐሳብ እነዚህን ርዕይ ያላቸውን
የንግዱ ኅብረተሰብ የሥራ አመራሮች ከተመረጡ
ከውጭ አገር አቻዎቻቸው ጋር የሚገናኙበትና
ጥምረት የሚፈጥሩበትን መንገድ ማመቻቸትና ማቀላጠፍ
ነው፡፡ የዓለም ኢኮኖሚ ፎረም በአፍሪካ
የሚያመጣቸው ዓለም አቀፍ የንግድና ኢንቨስትመንት
ኩባንያዎችና ኃላፊዎች፣ ከዚህም ቀደም ሲል
በአፍሪካ አኅጉር በተለያዩ እንቅስቃሴዎች ላይ
ኢንቨስት ያደረጉና በአኅጉሪቱ በኢንቨስትመንትና በቢዝነስ
ለመሰማራት ምን እንደሚያስፈልግ የሚያውቁ ናቸው፡፡
ያም በመሆኑ በዓለም ኢኮኖሚ ፎረም
በአፍሪካና በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ፎረም የሚሳተፉትን
የውጭ አገር ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ኢንቨስት
እንዲያደርጉ ማግባባት፣ በአሜሪካና በአውሮፓ ያሉ
ኢንቨስተሮችንና ከዚህ በፊት በኢትዮጵያ ኢንቨስት
አድርገው የማያውቁ ባለሀብቶች ለማምጣት ከመሞከር
የበለጠ ስኬታማ ሊሆን እንደሚችል ለመገንዘብ
የሚያዳግት አይመስለኝም፡፡ ስለሆነም ቢያንስ 200
የሚሆኑ ዓለም አቀፍ ዕውቅና ያላቸው
የውጭ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ፎረም
ይሳተፋሉ፡፡ እነዚህ ተሳታፊዎች ኢትዮጵያ ለኢኮኖሚ
ዕድገት ቅድሚያ በምትሰጣቸው ዘርፎች ላይ
የተሰማሩ ናቸው፡፡ እነዚህም ዘርፎች ግብርና፣
ኢንዱስትሪ፣ የማዕድን ፍለጋና የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ
ዘርፎች ናቸው፡፡ በመጨሻም በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት
ፎረም ላይ ከውጭ አገር የ200
ኩባንያዎች ተጠሪዎች ከአገር ውስጥም እንዲሁ
የ200 ኩባንያዎች ተጠሪዎች ተሳታፊ ይሆናሉ፡፡
ከእነዚህ በተጨማሪ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትና
አማካሪዎች የሚሳተፉ ሲሆን፣ ፎረሙም የሚከፈተው
በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ይሆናል፡፡
ተሳታፊዎች በኢትዮጵያ የቢዝነስና የኢንቨስትመንት ዕድል
ላይ በጥልቀት የሚወያዩ ሲሆን፣ የፎረሙም
ውጤት የአገሪቱን ገጽታ ከምግብ ፈላጊነትና
ተረጂነት ይልቅ ወደ የኢንቨስትመንት ዕድል
የነገሠባት አገር ገጽታ መቀየር ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ፕሪሳይስ ኮንሰልት ለሪፖርተር በላከው
መግለጫ የአፍሪካ ኢኮኖሚ እያደገና እየተፋጠነ
በመምጣቱ በአሁኑ ጊዜ የአኅጉሪቱ ኢኮኖሚ
“ላየን ኢኮኖሚ” እየተባለ እንደመጣና ከኢትዮጵያ
ኢኮኖሚ በላይ ያለ “ላየን ኢኮኖሚም”
እንደሌለ ተጠቅሷል፡፡ ይሁንና የዚህ ዓመት
የመጀመርያ ወራት ሪፖርት እንደሚያመለክተው ለኢንቨስትመንት
የተመዘገበው የካፒታል መጠን እንደቀነሰ ነው፡፡
ይኼን እንዴት ማጣጣም ይቻላል?
አቶ ሔኖክ፡- ስለተጠቀሱት ቁጥሮች አላወቅኩም፡፡ ስለ
ቁጥሮቹ ባውቅ ኖሮ የበለጠ ጠቃሚ
ይሆን ነበር፡፡ ይሁንና ይኼ ምንም
የሚያሳስበን ነገር አይደለም፡፡ ምክንያቱም የእኛ
ትኩረት ዘላቂ፣ የረጅም ጊዜና ውጤታማ
ኢንቨስትመንትን ወደ አገር ውስጥ መሳብ
ነው፡፡ እኛ እንደምናየውና እንደምናስበው የኢትዮጵያ
ኢኮኖሚ በመጪዎቹ ዓመታት ለብዙ ሰዎች
ብዙ የኢንቨስትመንት ዕድል የሚከፍት የአንበሳ
ኢኮኖሚ ነው፡፡ ስለሆነም ወደፊት ወደ
አገር ውስጥ የሚመጣው የውጭ ኢንቨስትመንት
ከኢኮኖሚው የበለጠ ተጠቃሚ እንደሚሆን ምንም
ጥርጥር የለውም፡፡ እኛ በመመርያ ደረጃም
ቢሆን መጥቶ ወዲያው የሚመለስ የአጭር
ጊዜ ኢንቨስትመንትን አናበረታታም፡፡ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ
አሁንም ገና እያደገ በመሄድ ላይ
ያለ ኢኮኖሚ በመሆኑ እዚህም እዚያም
ችግሮች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ስለሆነም የተጠቀሱት
የኢንቨስትመንት ቁጥሮች መውረድ ከዚህ ጋር
ሊያያዝም ይችል ይሆናል፡፡ ይሁንና በኢኮኖሚው
ዙርያ በዋነኛነት ጥላውን ያጠላው የዓለም
ወይም የአውሮፓ የወቅቱ የኢኮኖሚ ሁኔታ
መቀዝቀዝ ችግር ነው፡፡
ከዚህ ውጪ
ኢንቨስትመንት ኤጀንሲ የኢንቨስትመንት ምዝገባ ሪፖርት
አቀራረቡን የቀየረ ይመስለኛል፡፡ በመንግሥት በኩል
ከሚመዘገበው ይልቅ ወደ ግንባታ የተዘዋወሩ
ፕሮጀክቶች ላይ የበለጠ ትኩረት የሚደረግ
ይመስለኛል፡፡ ያም የቁጥሮቹን መውረድ አመላካች
ሊሆን ይችላል፡፡ የአገሪቱን የንግድና ኢንቨስትመንት
ሁኔታ ለማሻሻል አሁን ሥራ እየተሠራ
ነው፡፡ የበለጠ ኢንቨስትመንት ለመሳብ ብዙ
መሥራት ይጠበቅብናል፡፡ በተለይ ከንግድ አሠራር
ደንብ ጋር በተያያዘ አንዳንድ ጉዳዮች
አደጋ እንዳያስከትሉ መጠንቀቀ መቻል አለብን፡፡
እያደግንም ወደፊት ስንራመድ መንግሥትና የግሉ
ዘርፍ ተቀራርበው መሥራትና የንግድና ኢንቨስትመንት
አየሩን የበለጠ ማሻሻል አለባቸው፡፡ አንደኛው
አገሪቱ የውጭ ኢንቨስትመንትን ልትስብ የምትችለው
85 ሚሊዮን ተጠቃሚ ሕዝብ ያላት
በመሆኑ ነው፡፡
ይሁንና ያ እንደ
ቀድሞው የተለየ ነገር አይደለም፡፡ ከኢትዮጵያ
በስተደቡብ ያሉ አምስት ወይም ስድስት
የምሥራቅ አፍሪካ አገሮችን ያየን እንደሆን
ራሳቸውን በማስተሳሰራቸው 100 ሚሊዮን ተጠቃሚ
ሕዝብ ያለበት ክልል ወይም ቀጣና
ፈጥረዋል፡፡ የውጭ ባለሀብቶችን የሚስብ ሥርዓት
ፈጥረዋል፡፡ እኛ ዘላቂ በሆነ ሁኔታ
ተወዳዳሪነታችንን ማበልፀግ አለብን፡፡ ባለፉት አሥር
ዓመታት መሻሻል ብናሳይም በቀጣዩም የሚሠሩ
ሥራዎች ይጠብቁናል፡፡ ጊዜውም አሁን ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ስለ ውጭ ኢንቨስትመንት ከማውራታችን
በፊት በአገራችን ያለው የንግድና የኢንቨስትመንት
ሁኔታ ዳያስፖራውን ለመሳብ ምን ያህል
ምቹ ነው ይላሉ?
አቶ ሔኖክ፡- እርግጠኛ ሆኖ ለመናገር የንግድና
የኢንቨስትመንት ዕድሉ እንዳለ ግልጽ ነው፡፡
እዚህ ኢንቨስት ያደረጉ ቻይናዎች፣ ህንዶችና
ቱርኮች ውጤታማ መሆን ከቻሉ ዳያስፖራውም
ውጤታማ የማይሆንበት ሁኔታ አይታየኝም፡፡ ይህ
በእንዲህ እንዳለ ባለፉት ስድስትና ሰባት
ዓመታት በዳያስፖራው ላይ ያለኝ አስተያየት
ተቀይሯል፡፡ እኔ እንደሚመስለኝ ዳያስፖራውን ስናቀርብ
ተገቢ ጥያቄዎች ምላሽ በሚያገኙበት ሁኔታ
መሆን ይገባቸዋል፡፡ አስተሳሰባችንም ውጭ ባለው
ኢትዮጵያዊ ሁሉ ላይ ያተኮረ ሳይሆን፣
የተለያዩ ዓለም አቀፍ ኮርፖሬሽኖችን የሚመሩና
ነገሮችን የሚለውጡ ኢትዮጵያዊያን ላይ መሆን
ይገባዋል፡፡ ሌላው ማተኮር ያለብን እዚህ
እንዲመጡ ሳይሆን እዚያው ሆነው ለኢኮኖሚው
መጎልበት ማገዝ የሚችሉበትን ሁኔታ ማመቻቸት
ነው፡፡
እነዚሁ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን
የሚልኩትን ገንዘብ የበለጠ ጠቀሜታ እንዲኖረውም
ለማስቻል ፈጠራ የታከለበት የገንዘብ ማስተካከያ
ሥርዓት መፍጠርም የራሱ የሆነ ጠቀሜታ
ይኖረዋል፡፡ ይኼ ጉዳይ በሌሎች አገሮች
የሚሠራበትና እልባት የተሰጠው ጉዳይ ነው፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ በአሁኑ ጊዜ
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እያዘጋጀ ያለው
የዳያስፖራው ፖሊሲ ጠቀሜታ የሚኖረው ይሆናል፡፡
በጥቅሉ ለመናገር የአቀራረባችን ሁኔታ ካልሆነ
በስተቀር በትክክለኛው ጎዳና እየተጓዝን ነው፡፡
ሪፖርተር፡- እርስዎ የሚሉት ውጭ ባሉ
በተመረጡ ኢትዮጵያውያን ላይ ብቻ ማተኮር
ነው ውጤት የሚያመጣው ነው?
አቶ ሔኖክ፡- በመጀመርያ ደረጃ ውጤታማ ስለሆነ
ኢንቨስትመንትና ንግድ ስንነጋገር፣ እነዚህ የሚከናወኑት
በሥራ ፈጣሪዎች (አንትራፕሪነርስ) መሆኑን መገንዘብ
አለብን፡፡ በየትኛውም አካባቢ አንድ ላይ
በተሰበሰቡ ሰዎች መካከል ሥራ ፈጣሪዎቹ
በጣም አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ናቸው፡፡
በውጭ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያንም የሚንፀባረቀው ይኼው
ሀቅ ነው፡፡ እኔ እንደማስበው በኢትዮጵያ
ኢኮኖሚ ላይ ትርጉም ያለው ውጤት
ማምጣት የሚችለው ከዳያስፖራው አንድ በመቶ
የሚሆነው ብቻ ነው፡፡ ይኼ አንድ
በመቶ የሆነው ዳያስፖራ የአገሪቱን ኢኮኖሚ
በማሳደግና በማጎልበት ደረጃ ተአምር መሥራት
ይችላል፡፡ እናም እኔ የአገሪቱን ኢኮኖሚ
ለማሳደግ የማተኩረው በዚህ አንድ በመቶ
በሆነው ዳያስፖራ ላይ ነው፡፡ ቀሪውን
በአገሪቱ ፖለቲካና ማኅበራዊ ጉዳይ እንዲሳተፍ
ማድረግ ነው የሚለውን እመርጣለሁ፡፡
ሪፖርተር፡- በአሁኑ ጊዜ ከዚያ አንድ
በመቶ ከሆነው ዳያስፖራ ውጪ በአገር
ኢኮኖሚ ላይ እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው ምን
ያህሉ ነው ይላሉ?
አቶ ሔኖክ፡- ገና እየቧጠጥን ነው ማለት
ይቻላል፡፡ እንደሚመስለኝ በመጪዎቹ ዓመታት ብዙዎችን
የምናይበት ሁኔታ ይኖራል፡፡ አሁን እየታየ
ያለው ሁኔታም ቢሆን የሚያበረታታ ይመስለኛል፡፡
በአሁኑ ጊዜ በመንግሥት መሥርያ ቤትም
ሆነ በሲቪል ማኅበረሰብ ተቋማት፣ በግብረሰናይ
ድርጅት፣ በግሉ ዘርፍና በመሳሰሉት አንድ፣
ሁለት፣ አሥር ወይም ከዚያም በላይ
ዳያስፖራ ማግኘት ይቻላል፡፡ በነገራችን ላይ
እዚያው ባሉበት ሆነው ለአገሪቱ ዕድገት
ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረከቱ፣ ሆኖም ላበረከቱት
አስተዋጽኦ እኔ ነኝ ለማለትና ዕውቅናውን
ለመውሰድ ፍላጎት የሌላቸው በርካታ በውጭ
ያሉ ኢትዮጵያውያን አሉ፡፡ እነዚህ ናቸው
ወደፊትም አገሪቱን የሚለውጧት፡፡ እንዲያው ለመታየት
የሚሞክሩትን እንተዋቸውና፡፡